የሠልጣኝ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮቹ ቅሬታ!

የትራንስፖርት ገንዘብና በቂ ምግብ እየቀረበልን አይደለም ሲሉ ሠልጣኝ መምህራን ቅሬታ አቀረቡ።

“ችግሩ ተፈትቶ ገንዘባቸውም ምግባቸውም ተስተካክሏል። -የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት

በዩኒቨርሲቲዎችና በተለያዩ የማሠልጠኛ ማዕከላት የክረምት ስልጠና እየወሰዱ ያሉ መምህራን፣ የትራንስፖርት ወጪ ይሰጧችኋል ተብለው ቢፈርሙም፣ ገንዘብ እንዳልገባላቸውና የሚቀርብላቸው ምግብ በቂ እንዳልሆነ ተናገሩ፡፡

ከወልድያ፣ ዲላ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች ቅሬታቸውን ለሪፖርተር የተናገሩት መምህራን፤ ለትራንስፖርት ተብሎ የሚከፈላቸው ገንዘብ በቂ አለመሆኑንና ይሰጣችኋል ተብለው ከፈረሙ በኋላ ምንም ዓይነት ገንዘብ አልተከፈለንም ብለዋል፡፡

ስሜ እንዳይጠቀስ ያለ ከሰቆጣ አካባቢ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስልጠናውን እየተከታተለ ያለ መምህር ” ምግብና መኝታ ዩኒቨርሲቲው እያቀረበላቸው ቢሆንም፣ እየቀረበ ያለው ምግብ ግን ለበሽታ የሚያጋልጥ ነው” ብሏል፡፡

“ተማሪ እያለን እንደዚህ ዓይነት ምግብ ቀርቦልን አያውቅም” ያለው ቅሬታ አቅራቢው መምህር፤ ዩኒቨርሲቲው ያቀረበውን ምግብ በልቶ እስከ መታመም መድረሱን ገልጿል፡፡ ለትራንስፖርት ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣቱንና ይሰጣችኋል የተባለው የትራንስፖርት ክፍያ ወጪውን እንደማይሸፍንም አስረድቷል፡፡

“ስልጠናውን አቋርጠን ልንወጣ ነበር” ያለው ሌላው የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ሠልጣኝ መምህር፤ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ከመጡ ተወካዮች ጋር ቢነጋገሩም መፍትሔ ሳይሰጧቸው በተሰበሰቡበት ጥለዋቸው መሔዳቸውን ተናግሯል፡፡

ከ2,70ዐ በላይ ሠልጣኝ መምህራን መኖራቸውን የተናገረው አስተያየት ሰጪው፤ ከሩቅም ከቅርብም የሚመጡ ሠልጣኞች ተመሳሳይ የትራንስፖርት ክፍያ ይታሰብላቸዋል ብሏል፡፡

“ስልጠናው ከመንግሥት ጋር ቅሬታ እንዲኖረን ያደረገ ነው” ያለው መምህሩ፤ “ድርጊቱ መንግሥት ለመምህራን ያለውን ንቀት የሚያሳይ ነው” ሲል አክሏል፡፡

ለሚቆዩባቸው 21 ቀናት ሥልጠና የስድስት ቀናት ብቻ በቀን 4ዐዐ ብር አካባቢ እንደሚታሰብላቸው የተናገረው መምህሩ፤ ከዚህ ቀደም በነበረው የክረምት ሥልጠና ከዚህ የተሻለ አበል ይታሰብ እንደነበር አስታውሷል፡፡

በተመሳሳይ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የክረምት ስልጠና በመውሰድ ላይ የነበሩ ከ1,7ዐዐ በላይ መምህራን የትራንስፖርት ክፍያ ስላልተፈጸመላቸውና ዩኒቨርሲቲው እያቀረበ ያለው ምግብ ጥራት የጎደለው በመሆኑ ስልጠናውን አቋርጠው ለመውጣት ታዘጋጀው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከምግብና ከትራንስፖርት ባሻገር የመፀዳጃ ቤት እና የመኝታ ቤት ንፅህና መጓደል ሌላው ችግር እንደሆነባቸው የተናገሩት መምህራኑ፤ ከምግብ ጥራት መጓደል ጋር ተያይዞ አመፅ ተቀስቅሶ እንደነበርና ከአመፁ በኋላም የተወሰነ መሻሻል ታይቷል ብለዋል፡፡

የተነገራቸው የትራንስፖርት ክፍያ እንዳልደረሳቸውና በዚህም ችግር ውስጥ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

“የትራንስፖርት ክፍያ በወቅቱ ባለመከፈሉ ሠልጣኝ መምህራንን አበሳጭቷቸዋል” ሲሉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጉቼ ጉሌ (ዶ/ር) ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ክፍያው የዘገየበት ምክንያትም ሠልጣኞቹ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በመሆናቸው የማጣራት ሥራው ብዙ ጊዜ ስለወሰደባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“የክልል ትምህርት ቢሮ ችግራቸው በአፋጣኝ እንዲፈታ አድርጓል” ያሉት ጉቼ (ዶ/ር)፤ “ሁሉም መምህራን ክፍያው ተከፍሏቸዋል” ሲሉ አክለዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ይህንን ይበሉ እንጂ መምህራኑ የትራንስፖርት ሳይከፈላቸው ወደ መጡበት ሊመለሱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

መምህራኑ የትራንስፖርት አልተከፈለንም ብለዋል በማለት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ምናልባት ከመጡበት ርቀትና ለትራንስፖርት ካወጡት ገንዘብ ጋር የማይመጣጠን ወይም ይከፈለናል ብለው ካሰቡት ያነሰ ክፍያ ተከፍሏቸው ሊሆን ይችላል እንጂ ክፍያው ተፈጽሟል” ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የምግብ አቅርቦትን በተመለከተ መምህራኑ ላቀረቡት ቅሬታ ፕሬዝዳንቱ ሲመልሱ፣ ችግሩ መኖሩን አምነው፣ “እኛ የምንሠራው በተሰጠን የምግብ ዝርዝር መሠረት ነው” ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ተመሳሳይ ቅሬታዎችን ያነሱ ሠልጣኝ መምህራን በተለይ ከክፍያ ጋር ተያይዞ ችግር መኖሩንና ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡

የሠልጣኝ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮቹ ቅሬታ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to top